፲፫ ተመይጥ እግዚኦ እስከ-ማእዜኑወተናበብ በእንተ-አግብርቲከ
ባለፈው ክታብ እንዳየነው "እምግርማ መዐትከ ኀልቁ" ብሎ የፍዳ-ፄዋዌን (የምርኮውን መከራ) ጽናት ካጦዘው በዃላ አኹን ይጠመዝዛል፦ "ተመይጥ" ብሎ። አቤቱ ከመዐት ወደምሕረት ተመለስ እንጂ፤ የማትመለስ እስከ መቼ ነው? ተመለስና ስለባሮችኽ ስለትሩፋን ተናገር፤ ተናገር እንጂ የማትናገር እስከ መቼ ነው? ወተናበብ (ተናገር) ሲል ግን፦ "ስጠኝ ፈጆታ" ማለት አይደለም (ከርሱ በላይ የሚፈርድ ዳኛ ኖሮበት፤ ርሱ እንደጠበቃ የሙግት፣ የክርክር ፈንታ፣ ተራ፣ ፈረቃ ይሰጠኝ የሚል አይደለም)፤ የግብር ሙግት ነው፤ "ፍረድ" ሲል ነው።
ከመዐት ሲጠመዘዙ ወደምሕረት፣ ከፄዋዌ ሲጠመዘዙ ወደሚጠት ማቅናት ነውና ከዚህ በዃላ የምሕረትን የሚጠትን ጣዕም ያወሳል።
፲፬ እስመ-ጸገብነ በጽባሕ ምሕረተከተፈሣሕነ ወተሐሠይነ በኵሉ መዋዕሊነ፲፭ ወተፈሣሕነ ህየንተ-መዋዕል ዘአሕመምከነወህየንተ-ዓመት እንተ-ርኢናሃ ለእኪት፲፮ ርኢ ላዕለ-አግብርቲከ ወላዕለ-ተግባርከ እግዚኦወምርሆሙ ለደቂቆሙ፲፯ ለይኵን ብርሃኑ ለእግዚአብሔር አምላክነ ላዕሌነወይሠርሕ ለነ ተግባረ-እደዊነ።
"ሰባ ዘመን መከራ ስለተቀበልነ ፈንታ፣ ሰባ ዘመን የመከራዋን ጽናት ስላየነ ፈንታ፣ በሰባ ዘመን እንደንጋት ደስ የሚያሰኝ ቸርነትኽን አግኝተናልና ደስ አለን" ብሎ ፍዳን ከጨረሱ ወዲያ የምትገኝ ምሕረት ቸርነት እንዴት እንደምትጥም ይናገራል። ደግሞም፤ አንዳንድ ሰነፎች እንደሚያስቡት ሳይኾን የአበው ሥራ ለልጆች የሚተርፍ የሚበጅ ነውና፤ "አግብርቲከ... ተግባርከ፦ ደጋጎቹን አብርሃም፣ ይስሐቅ፣ ያዕቆብን አይተኽ ደቂቆሙ፦ ልጆቻቸውን ትሩፋንን ከባቢሎን መርተኽ ወደኢየሩሳሌም አውጣቸው" ይላል፤ በምልጃ በተደገፈ ጸሎት። አያይዞም የፈጣሪያችን የእግዚአብሔር ብርሃኑ በላያችን ይብራልን፤ ረድኤቱ፣ ሚጠቱ ይደረግልን። ካለ በዃላ፦ "እንዲህ የኾነ እንደኾነ፤ወይሠርሕ ለነ ተግባረ-እደዊነ፦ የእጃችን ሥራ የቀና ይኾናል፤ ማለት የተከልነው ይጸድቃል፣ የዘራነው ይበቅላል፤ በቀኝ እጃችን መወርወር በግራ እጃችን መመከት ይኾንልናል።" ብሎ ይደመድማል።
ትሩፋንን የሚመለከተው ዐይነተኛው ትርጕም ይህ ኾኖ ሌላም አወራረድ አለው። ወደራሳችን ሕይወትም ተገልብጦ ሊተረጐም ይችላል። እንመለስበታለን።