በዚህ ደስ የሚለው ደግሞ ደጋግሞ ደስ ይበለው፤ የሚከፋው ካለ ግን የደስታ መንፈስ ያድለው፤ ማንም ይውደድ ማንም ይጥላ ታኅሣሥ ፳፱ ቀን የድንግልም በዓሏ ነው። እስኪ ይህንን እመቤታችን ማርያም የተናገረችው የወንጌል ቃል ልብ እንበለው፦ "እስመ-ገብረ ሊተ ኀይለ ዐቢያተ" (ደግ ነገር/ድንቅ ተአምር ሠርቶልኛልና)። ምን ማለት ነው?
ምን ተሠራ?
ሊዘከር የሚገባው ደግ ሥራ። አይደለምን?
ማን ሠራው?
ባለቤቱ፣ እግዚአብሔር። አይደለም እንዴ?
ለማን ሠራው?
ለድንግል ማርያም። አይደለም እንዴ?
እንዴታ፣ ነው እንጂ!
ስለኾነም በቅጥነተ-ልብ ለሚመለከት የጌታ መወለዱ የድንግል መውለዷ አንድ እና ያው ክሥተት ነው። ነውና፤ የመወለዱ በዓል ያው የመውለዷ በዓል ነው። እናም ይህንን ምስጢር ለማሳየት ስንል፦ ግእዝ ላልጠገበ ጆሮ እንደሚሻክር እያወቅነው ብቻ ሳይኾን፤ የት ለመድረስ እንደሚቸኩል ባንረዳውም "ለብርሃነ-ልደቱ" ማለት እንኳ እንደሚረዝምበት/እንደሚንዛዛበት በምንገምተው ትውልድ ውስጥ እንዳለን ሳንስተው "እንኳን ለ'በዓለ-ወሊዶታ ለድንግል ዐማኑኤልሃ' አደረሰን" እንላለን። "እንኳን 'ድንግል ዐማኑኤልን መውለዷ ለሚታሰብበት በዓል' አደረሰን" ማለት ነው።
በዚህም "ኦድ" እንመስል ይኾናል፤ ከቅዱሳት መጻሕፍት ቃል፣ ከአበው ዐሳብ ግን አንርቅም። "ናሁ ድንግል ትፀንስ ወትወልድ ወልደ"ን ያስታውሷል። ከዚህም ጋር "እምየ" አባ ጊዮርጊስ በዚህ ዐቢይ በዓል እንዲነበብ በወሰኑት ድርሰት መጨረሻ እንዲህ ብለው ነበር፦
ዘንተ መጽሐፈ አዘዘ [ጊዮርጊስ]ይህም ማለት፦
ከመ-ይትነበብ በዕለተ-ተዝካራ[ለማርያም]
አመ ፳ወ፱ (ዕሥራ ወተሱዑ) ለታኅሣሥ
እንተ-ባቲ አስተርአየ ዕበየ-ክብራ
ወተሰብሐ ሥነ-ምግባራ
ለዓለመ-ዓለም። አሜን ወአሜን።
[ጊዮርጊስ] ይህ መጽሐፍ፦ማለት ነው።
[የማርያም] የክብሯ ታላቅነት በታየባት
የምግባሯ ውበት/ብቃት
በተገለጠባት/ባንጸባረቀባት
[የመውለዷ] መታሰቢያ በሚኾንባት ዕለት
በታኅሣሥ ፳፱ እንዲነበብ አዘዘ።
ለዘላለሙ። አሜን፣ አሜን።
ቸር ዐውደ-ዓመት ያውለን። ለብርሃነ-ልደቱ በሰላም እንዳደረሰን፤ ለብርሃነ-ጥምቀቱ በደኅና ያድርሰን። አሜን።