በገነት አትክልት ነገር፦() ጣዕም፣ () ልማላሜ፣ () ጽጌ፣ () ሥን፣ () ፍሬ፣ () መዐዛ፣ () ቈጽል፣ ይገኛል። እንዲሁም በመዝሙረ-ዳዊት ነገር፦ () አፍቅሮ-ጸላዕት፣ () ትሕትና፣ () ሃይማኖት፣ () ተስፋ-መንግሥተ-ሰማያት፣ (፭) ተአምኖ-ኀጣውእ፣ () ስርየት፣ () ምጽዋት ይገኛል።

Friday, September 28, 2012

መዝሙር ስለ ፄዋዌ እና ሚጠት



ፄዋ ባቢሎን ይብሉከ ሶበ በጸሖሙ መከራ
በምድረ ነኪር አፅራዕነ ስባሔ እስከ ሰቀልነ እንዚራ
ወአመ ሜጥኮሙ ክርስቶስ ምስለ ዘሩባቤል መልአከ ሐራ
በክልኤ ዓመት እመንግሥተ ዳርዮስ ዳራ
ሰብሑከ በመዝሙር ዘዐሥር አውታራ

ትርጉም፦
 
የባቢሎን ምርኮኞቸ አሉኽ በደረሰባቸው ጊዜ መከራ
ምስጋናን አቋረጥን በባዕድ አገር እስከ መስቀል ደርሰን እንዚራ
በመለስካቸውም ጊዜ ክርስቶስ ካለቃ ዘሩባቤል ጋራ
በኹለተኛ ዓመት መንግሥቱ ለንጉሥ ዳርዮስ ዳራ
አመሰገኑኽ በበገና በባለዐሥር አውታራ

Saturday, September 15, 2012

ዐውደ-ፄዋዌ

በእግዚአብሔር ፈቃድ በዚህ ምክታብ የጀመርነውን ትምርት በትጋት ሊከታተሉት የሚሹ ስላገኘን፤ እንዳዲስ ልንቀጥልበት ተነሥተናል። ለዛሬ ርእሱን ስትኮረኩሙ የምታገኙትን የትሩፋንን ኹናቴ የሚያሳይ ነገር ለጥፈናል። ማብራሪያውን በፓልቶክ ጉባኤ እንሰጣለን። "የኢ.ኦ.ተ.ቤ.ክ. የፍቅርና የሰላም ቤት" በሚባለው ክፍል። ቸር ያገናኘን።

Sunday, July 10, 2011

እግዚኦ ጸወነ ኮንከነ (ትርጕም 4)

ተመይጥ እግዚኦ እስከ-ማእዜኑ
ወተናበብ በእንተ-አግብርቲከ

ባለፈው ክታብ እንዳየነው "እምግርማ መዐትከ ልቁ" ብሎ የፍዳ-ፄዋዌን (የምርኮውን መከራ) ጽናት ካጦዘው በዃላ አኹን ይጠመዝዛል፦ "ተመይጥ" ብሎ። አቤቱ ከመዐት ወደምሕረት ተመለስ እንጂ፤ የማትመለስ እስከ መቼ ነው? ተመለስና ስለባሮችኽ ስለትሩፋን ተናገር፤ ተናገር እንጂ የማትናገር እስከ መቼ ነው? ወተናበብ (ተናገር) ሲል ግን፦ "ስጠኝ ፈጆታ" ማለት አይደለም (ከርሱ በላይ የሚፈርድ ዳኛ ኖሮበት፤ ርሱ እንደጠበቃ የሙግት፣ የክርክር ፈንታ፣ ተራ፣ ፈረቃ ይሰጠኝ የሚል አይደለም)፤ የግብር ሙግት ነው፤ "ፍረድ" ሲል ነው። 

ከመዐት ሲጠመዘዙ ወደምሕረት፣ ከፄዋዌ ሲጠመዘዙ ወደሚጠት ማቅናት ነውና ከዚህ በዃላ የምሕረትን የሚጠትን ጣዕም ያወሳል።
እስመ-ጸገብነ በጽባሕ ምሕረተከ
ተፈሣሕነ ወተሐሠይነ በኵሉ መዋዕሊነ
ወተፈሣሕነ ህየንተ-መዋዕል ዘአሕመምከነ
ወህየንተ-ዓመት እንተ-ርኢናሃ ለእኪትርኢ ላዕለ-አግብርቲከ ወላዕለ-ተግባርከ እግዚኦ
ወምርሆሙ ለደቂቆሙ
፯ ለይኵን ብርሃኑ ለእግዚአብሔር አምላክነ ላዕሌነ
ወይሠርሕ ለነ ተግባረ-እደዊነ።
"ሰባ ዘመን መከራ ስለተቀበልነ ፈንታ፣ ሰባ ዘመን የመከራዋን ጽናት ስላየነ ፈንታ፣ በሰባ ዘመን እንደንጋት ደስ የሚያሰኝ ቸርነትኽን አግኝተናልና ደስ አለን" ብሎ ፍዳን ከጨረሱ ወዲያ የምትገኝ ምሕረት ቸርነት እንዴት እንደምትጥም ይናገራል። ደግሞም፤ አንዳንድ ሰነፎች እንደሚያስቡት ሳይኾን የአበው ሥራ ለልጆች የሚተርፍ የሚበጅ ነውና፤ "አግብርቲከ... ተግባርከ፦ ደጋጎቹን አብርሃም፣ ይስሐቅ፣ ያዕቆብን አይተኽ ደቂቆሙልጆቻቸውን ትሩፋንን ከባቢሎን መርተኽ ወደኢየሩሳሌም አውጣቸው" ይላል፤ በምልጃ በተደገፈ ጸሎት። አያይዞም የፈጣሪያችን የእግዚአብሔር ብርሃኑ በላያችን ይብራልን፤ ረድኤቱ፣ ሚጠቱ ይደረግልን። ካለ በዃላ፦ "እንዲህ የኾነ እንደኾነ፤ወይሠርሕ ለነ ተግባረ-እደዊነ፦ የእጃችን ሥራ የቀና ይኾናል፤ ማለት የተከልነው ይጸድቃል፣ የዘራነው ይበቅላል፤ በቀኝ እጃችን መወርወር በግራ እጃችን መመከት ይኾንልናል።" ብሎ ይደመድማል።

ትሩፋንን የሚመለከተው ዐይነተኛው ትርጕም ይህ ኾኖ ሌላም አወራረድ አለው። ወደራሳችን ሕይወትም ተገልብጦ ሊተረጐም ይችላል። እንመለስበታለን። 
 

Tuesday, May 31, 2011

እግዚኦ ጸወነ ኮንከነ (ትርጕም 3)

ኢትሚጦ ለሰብእ ለሳር
ወትቤ ተመየጡ ደቂቀ-እጓለመሕያው...
ወዓመቲነኒ ከመ-ሣሬት ይከውና።
ወመዋዕለ-ዓመቲነኒ ክራማት
ወእመሰ በዝ ሰማንያ ዓም
ወፈድፋዶንሰ እምእላ ፃማ ወሕማም
እስመ-ለፈት የውሀት እምኔነ፤ ወተገሠጽነ።
መኑ የአምር ይለ-መቅሠፍትከ
እምግርማ መዐትከ ልቁ።
ከመዝ አርኢ የማነከ 
ለምሁራነ-ልብ በጥበብ።

ባለፈው "...ከኹሉ አስቀድሞ የነበርኽ፤ ዓለምንም አሳልፈኽ የምትኖር አንተ ነኽ 'ኮ! አንተ ነኽና..." በማለት ጅምሩን "ሰብከን" (ሞከር አድርገን) አቆይተነው ነበር። (ባንድምታ ትምርት እንደነገ ጥልቅ ትምርቱ ሊቀጥል እንደዛሬ አርእስተ-ነገሩን ሞክሮ መተው "መስበክ" ይባላል።) እስኪ ባለፈው በሰበክነው ላይ ጥቂት እንቀጥል።

ከኹሉ አስቀድሞ የነበርኽ፤ ዓለምንም አሳልፈኽ የምትኖር አንተ ነኽ 'ኮ! አንተ ነኽና፦ ኢትሚጦ ለሰብእ ለሳርሳርን ለሰው ሰውን ለሳር አሳልፈኽ አትስጠው። አንተ ወትቤ ተመየጡ ደቂቀ-እጓለመሕያው ከገቢረ-ጢአት ወደገቢረ-ጽድቅ፣ ከአምልኮ-ጣዖት ወደ አምልኮ-እግዚአብሔር ተመለሱ፤ እኔም ከመዐት ወደምሕረት እመለስላችዃለኹ ብለኻልና፤ እኛም...ተመልሰናልና አንተም...ተመልሰኽ ይቅር በለን። 
ለነገሩማ ጥንቱን መበደላችን ቅሉ እኛንስ ምን ሊጠቅመን አንተንስ ምን ሊጎዳኽ ወዓመቲነኒ ከመ-ሣሬት ይከውና፦ ዘመኖቻችን እንደሸረሪት የኾኑ ምናምንቴዎች አይደለንምን? ሸረሪት ከእሳት የገባች እንደኾነ አጥንት ጕልጥምት የላትም ቀልጣ ትጠፋለች እኛስ ከሞትን በዃላ መች የት ደረሰ እንባላለን! (እዚህ ላይ ትሩፍ በፍጹም ልቡ አምኗልና አምላኩ "ብሑተ-ህላዌ" እንደነው/እንደኾነ በተረዳው መጠን የራሱም "ንዴተ-ህላዌ" እንዴት ጠልቆ እንደገባው ልብ ይሏል።)

ከዚህ በዃላ ወደጊዜያዊ ችግሩ ተመልሶ "ነቢያት እንደተናገሩ፦ በባቢሎን የምንኖረው ሰባ ዘመን ነው፤ ከዚያም ዕልፍ ቢል ሰማንያ ዘመን ነው። ከሰማንያ ዘመን በዃላ ግን ጻር ጋር ነው፤ ከዚህ ከቀረ መቅረቱ ነውና።" በማለት የምርኮውን ዘመን ይጠቅሳል። ያም ሊኾን የቻለው ባለፈው እንዳተትነው በገዛ ጥፋቱ መኾኑን ይገልጥና የቅጣቱንም አግባብነት እንዲህ ሲል አጕልቶ ይናገራል፦ መኑ የአምር ይለ-መቅሠፍትከ[እንዲያ በድለን] መከራ ባታመጣብን መቅሰፍትኽን የምታመጣበት ይልኽን ማን ባወቀው ነበር።ከዚሁ አያይዞ መከራው በአሕዛብ (በባቢሎናውያን) አማካይነት መምጣቱ በአሕዛብ የበላይነት በሕዝበ እግዚአብሔር (በእስራኤል) የበታችነት ሳይኾን፤ እነርሱም (አሕዛቡ፣ ባቢሎናውያኑ) ፍጡራንኽ እንደመኾናቸው በመሣሪያነት በተጠቀምኽባቸው ባንተው ፈቃድ ነው ለማለት እምግርማ መዐትከ ልቁ፦የተፈጸምነውስ ያንተ ቁጣ ከመገለጡ የተነሣ ነው ይላል። ይኸውም ያንተ ቀኝ ያንተ ሥልጣን ሥራ መኾኑን ከመዝ አርኢ የማነከ ለምሁራነ-ልብ በጥበብ ጥበብን ሕግን ለምናውቅ ለእኛ ግለጥልን በማለት አያይዞ ይለምናል። 

ተመይጥ እግዚኦ እስከ-ማእዜኑ?
ወተናበብ በእንተ-አግብርቲከ... ይቆየን።

Saturday, May 14, 2011

እግዚኦ ጸወነ ኮንከነ (ትርጕም 2)

እግዚኦ ጸወነ ኮንከነ። ዘእንበለ-ይቁም አድባር ወይትፈጠር ዓለም ወምድር፤ እምቅድመ-ዓለም ወእስከ-ለዓለም አንተ ክመ
እስመ-ለቅነ በመዐትከ፤ ወደንገጽነ በመቅሠፍትከ።
ወሤምከ ጢአተነ ቅድሜከ፤ ወዕሉምነሂ ውስተ-ብርሃነ-ገጽከ።
፲ ...እስመ-ለፈት የውሀት እምኔነ፤ ወተገሠጽነ።
ባለፈው ክታባችን ርእሱ ላይ ያተኮርንበት ምክንያት አኹን ግልጽ እንደሚኾን ተስፋ እናደርጋለን። በተለይ ከአንድ ሌላ ርእስ ጋራ አነጻጽረን ስናየው።  እንደሚከተለው፦ 

በውጭው ዓለም በመዝሙረ-ዳዊት ጥናት የተጠመዱ ምሁራን ከመዝሙረ-ዳዊት ዐልፎ ለመላው ቅዱሳት መጻሕፍት፤ ለሌሎች ሥነ-ጽሑፎችም ጭምር የሚጠቅም የትርጓሜ ስልት ፈጥረዋል። ከነዚህ ስልቶች በዋናነት የሚጠቀሰው "Formgeschichte/Formkritik = Form-historical/Form-critical" (የቅርፅ ታሪክ/ዐተታ) ወይም "Gattungsgeschichte/Gattungskritik = Type-historical/Type-critical" (የዐይነት ታሪክ/ዐተታ) የሚሉት ነው።  ከዚህ ስልት ጋር በተያያዘ የሚጠሩ ታላላቅ ስሞችን ለማስተዋወቅ ያኽል ጀርመናዊውን ኸርማን ጕንክልን እና ኖርዌያዊውን ዚግመንድ ሞቪንክልን መጥቀስ ይቻላል። ታዲያ በነዚህ ታላላቅ ምሁራን ላይ የተመሠረተው ጥናት የደረሰበት የመዝሙር ፹፱ ዐይነቱ (ፎርሙ፣ ታይፑ)፦ "community prayer song" (የማበር ጸሎት መዝሙር) የሚል ነው ( ሌሎችም ዐይነቶች  ይጠቀሳሉ፤ ለጊዜው እንለፋቸው)። በዚሁ ስልት መሠረት እንደተወሰነው፤ የመዝሙሩ ዐይነተኛ መልእክትም የሰውን ዐላፊ ጠፊነት እና የእግዜርን ዘለዓለማዊነት ማስተማር ነው። ማለፊያ አይደለም? ነው እንጂ፤ ልዩነት እና ጥልቀት (specificity and depth) ግን ይጎድለዋል።

ወደኛ ስንመጣስ? እንግዲህ ለኛ ዋናው ቊልፋችን "በእንተ-ትሩፋን" የሚለው ርእስ ነው ብለናል። መዝሙሩን በዚህ ርእስ ከፍተን ስንገባ ምን እናገኛለን? ማለትም፤ ከትሩፋን ጋር ያለውን ትይይዝ መገንዘባችን ከላይኛው ትርጕም የተለየ ምን ትርፍ ይሰጠናል? በትግሥት እንከታተል።

እስራኤልን ለምርኮ ያበቃቸው፤ ተራ ጥፋት፣ ጥቃቅን ጢአት አልነበረም። ለእስራኤል ምርኮ ለኢየሩሳሌም መጥፋት ዋና ምክንያቱ አምላካቸው እግዚአብሔርን መተዋቸው ይልቁንም አድባር አውግር ማምለካቸው ነበር። ይኸውም ለነቢዩ ኢሳይያስ አስቀድሞ ተገልጦለት በትንቢቱ የመጀመሪያ ምዕራፍ እንዲህ ብሎ ነበር፦

፩፡፬ እፎ ደግምዎ ለእግዚአብሔር።
(እግዚአብሔርን እንዴት ተዋችኹት? እንዴት ተዋችኹት? እንዴት ተዋችኹት?)

በዚህም ምክንያት እግዚአብሔር እንደሚቆጣ፣ መከራም እንደሚመጣባቸው በብዙ ቦታ፤ እዚያውም በቊጥር ነግሯቸዋል፦
 ኵሉ ርእስ ለሕማም። ወኵሉ ልብ ለዘን። (የሰው ኹሉ ራስ ለመገጠብ ይኾናል። [ተማርከው በሚኖሩበት] ትብትብ ምንጣፍ በመሸከም። አንድም...ንጉሡ ለመከራ፣ ሊቀ-ካህናቱ/ነቢዩ ለዘን ይኾናል። አንድም... ልዑላኑ ለመከራ፣ ዐዋቆቹ ለዘን ይኾናሉ።)
በምርኮው ጊዜ የነበረው ነቢይ ዳንኤልም እንዲህ ብሏል፦ 
፡፳፰- ...እስመ-በኵነኔ-ጽድቅከ አምጻእከ ዘ ኵሎ በእንተ-ጢአትነእስመ-አበስነ ወጌገይነ ደግናከ
(ስለ ጢአታችን ይኽን ኹሉ ፈርደኽ አምጥተኽብናልና፤ አንተን በሕግ በአምልኮት የተውንኽ እኛ ፈጽመን በድለናልና።)
ይልቁንም ስለኢየሩሳሌም መጥፋት እና ስለሕዝቧ መማረክ ልቅሶውን (ሰቆቃውን) ጭምር የጻፈልን ኤርምያስ እያተትነው ያለውን ነገር ቊልጭ አድርጎ ያሳየናል (ከምዕራፍ በረጅሙ እንጥቀስ)፦

ከመዝ ይቤ እግዚአብሔር፦
ምንተ ረከቡ አበዊክሙ ላዕሌየ በዘይግዕዙኒ ከመ-ይርሐቁ እምኔየ ነዋ? (ከኔ ፈጽመው ይርቁ ዘንድ፣ እኔን በሚነቅፉ ገንዘብ፣ እኔን የሚነቅፉበት አባቶቻችኹ በኔ ምን ተዋርዶ ምን ነቀፋ አገኙብኝ?)
ወሖሩ ወተለው ከንቶ (ኼደው ከንቱ ጣዖትን ተከተሉ፤ ከንቱ ጣዖትን አመለኩ።)
ወከንቶ ኮኑ። (እነሱም ከንቱ ኾኑ)...
ኪያየ ደጉኒ ነቅዐ-ማየ-ሕይወት (የሕይወት የረድኤት መገኛ እኔን በሕግ በአምልኮ ተውኝ)
ወከረዩ ሎሙ አዘቃተ ንጹፋተ ዘአልቦ ማይ። (እኔን ትተው ሕይወት ረድኤት የማይገኝበት ጣዖቱን አመለኩ)...
ናሁ ርእዪ ዘረሰየኪ ዲገ-ዚአየ። ይቤ እግዚአብሔር አምላክኪ። (ፈጣሪሽ እግዚአብሔር "እኔን መተውሽ ያደረገሽን ማድረግ እነሆ እዪ" አለሽ)
ተአምሪ ወትጠይቂ ከመ-ይመርረኪ ዲገ-ዚአየ ይቤ እግዚአብሔር አምላክኪ። ("እኔን በሕግ በአምልኮ መተውሽ መከራውን እንዲያመጣብሽ ዃላ ታውቂያለሽ ትረጅዋለሽ" አለሽ)...
ወትቤሊ ኢገበርኩ (አንቺ ግን ጢአት ሠርተሽ አልሠራኹም ትይኛለሽ።)
ዳዕሙ ተሐውሪ ውስተ-አድባር ነዋ (ጢአት ለመሥራት ጣዖት ለማምለክ ወደረጃጅሙ ተራራ ትኼጃለሽ። በተራራ ያመልካሉና፤ አንድም በተራራ የቆመውን ያመልካሉና...)
ወታሕተ-ኵሉ ዖም ዘቦ ጽላሎት (ጥላ ወዳለው ዛፍ ትኼጃለሽ)
ወበህየ ከዐውኪ ዝሙተኪ። (ከዚያውም ቦታ ዝሙትሽን አብዝተሽ ሠራሽው)...
እስመ-ልቈ-አህጉራቲከ አማልክቲከ ይሁዳ። ("ይሁዳ!" ብሎ ያሰማዋል፦ "የጣዖቶችኽ ቊጥር ባገሮችኽ ቊጥር ልክ ነውና")
ይህ እንዲህ ነው፤ በዚህም መሠረት በመዝሙር ፹፱ የምንሰማውን የ"ትሩፍ" ድምፅ ለመተርጎም እንሞክር።ትሩፍ በቊጥር ፦ "እስመ-ለፈት የውሀት እምኔነ፤ ወተገሠጽነ።"  ሲለን፤ "...ሕግ መጠበቅ (ሃይማኖት) ከኛ ጠፍቷልና፤ በመከራው ተገሠፅን" ማለቱ እንደኾነ እንረዳለን። በቊጥር እንደተገለጸው ደግሞ፦ "እኛ ጢአቱን፣ አምልኮተ-ጣዖቱን በየተራራው፣ በየኮረብታው ተሸሽገን ስንፈጽመው አንተ የማታይብን ቢመስለንም፤ አንተ ግን ታየን ኖሯል" ለማለት "ወሤምከ ጢአተነ ቅድሜከ፤ ወዕሉምነሂ ውስተ-ብርሃነ-ገጽከ።"  (ጢአታችንን በፊትኽ አኖርኽ፤ ማለት ታውቀዋለኽ። ተሸሽገን የሠራነው በደላችንም በፊትኽ ብርሃን ወለል ብሎ ይታያል፡) ይላል። [እዚህ ላይ ጽርኡን/ግሪኩን ተከትሎ የተሳሳተውን የግእዝ ንባብ በዕብራይስጡ ተመርጕዘን አርመነዋል፡ "ዓለም"ን "ዕሉም" ብለን።] እንዲህ ጢአታችን ወለል ብሎ በመታየቱ፣  አንተም በመቆጣትኽ  "...ለቅነ በመዐትከ፤ ወደንገጽነ በመቅሠፍትከ።" በመዐትኽ ተፈጸምን፤ በመቅሠፍትኽም ደነገጥን (ኢየሩሳሌም ጠፋች፣ እኛም ተማረክን)።...

ልብ እንበል፤ በመዝሙሩ ውስጥ ድምፁን የምንሰማው "ትሩፍ" የዚህ ታሪክ ባለቤት የነበረ "ተነሳሒ" እስራኤላዊ ነው (በነጠላም ይኹን በብዙ ምስጢሩ አይቀየርም)። ንስሐውም በደሉን ሲፈጽም አለማስተዋሉን በመገንዘብ፣ አኹን ግን ልብ ማድረጉን በማሳየት ሊኾን ይገባዋልና፤ መዝሙሩን ሲጀምር ቅሉ እንዲህ ብሎ ነው የጀመረው፦ "እግዚኦ ጸወነ ኮንከነ" እንዲያው የመታለል ነገር ኾኖ እንጂ፤ ዱሮውንም'ኮ ከትውልድ እስከትውልድ አምባ መፀጊያችን አንተው ነበርኽ። "ዘእንበለ-ይቁም አድባር ወይትፈጠር ዓለም ወምድር፤ እምቅድመ-ዓለም ወእስከ-ለዓለም አንተ ክመ" ወይ ሞኝነታችን፣ ወይ አበሳችን፣ ወይ በደላችን!፦ እሊያ አንተን ትተን ልናመልካቸው የሞከርናቸው አድባር-አውግሩ፣ መጥፎ ግብራቸውን በተከተልንላቸው በአሕዛብ ዘንድ አድባሩን አውግሩን እንደወለደች ትታመን እና የሕይወት እናት ተብላም ትመለክ የነበረችው ምድርም፣  ዓለም ቅሉ በሞላው እንጂ (!) ሳይፈጠሩ፤ ከኹሉ አስቀድሞ የነበርኽ፤ ዓለምንም አሳልፈኽ የምትኖር አንተ ነኽ 'ኮ! አንተ ነኽና... (እጅግ የተመቸ የትርጕም አግጣጫ አልያዝንም?)
እዚህ ይቆየን፤ እንቀጥላለን...




Tuesday, May 3, 2011

እግዚኦ ጸወነ ኮንከነ (ትርጕም)

"እግዚኦ ጸወነ ኮንከነ"ን (፹፱ኛውን መዝሙር) እዚህ ለጀመርነው ሥራ መቃናትም ኾነ ለሕይወታችን እንድንጸልየው በማሳሰብ ንባቡን በምልክት አዘጋጅተን ከኛው ክታባችን ጋራ አያይዘን አቅርበነዋል (አኹንም በድጋሚ አያይዘነዋል)። በቀደመው ክታባችን እንድናያይዘው መነሻ የኾነን "ፈጻሚ እንጂ ጀማሪ ብቻ አያድርጎት" የሚለው ያንድ ወዳጃችን ምኞት እና ጸሎት ነበር።  አኹን ደግሞ የትርጓሜ ልምምዳችንን በዚሁ መዝሙር ለመጀመር ስላሰብን ዘሩን በቅርቡ እንድናገኘው ነው። እነሆ ዘሩን ደጋግመን እያነበብን ትርጕሙንም ቀስ እያልን እናኺደው።

በዚች ክታብ ሊያጋጥሙን የሚችሉትን የሚከተሉትን ስያሜዎች ልብ እንድንላቸው፦ 
  • ማኼድ = the process of interpretation
  • ዘር = the verse/passage to be interpreted
  • የሊቅ ዘር = the version (of the verse/passage) preferred by scholars
  • ዘይቤ = literal interpretation
  • አንድም = introduces alternative interpretation
  • ቀጠፋ = excerption
  • ርእስ/አርእስት = title/theme
  • በእንተ- = on/about...
"እግዚኦ ጸወነ ኮንከነ" በርእሱ "በእንተ-ትሩፋን፤ ጸሎቱ ለሙሴ ብእሴ-እግዚአብሔር" ይላል። ይህም ማለት፦ (1) ስለ-ትሩፋን፤ (2) የእግዚአብሔር ሰው የሙሴ ጸሎት፤ ማለት ነው። "ትሩፋን" የሚባሉት በባቢሎን ምርኮ "አበው አልቀው የቀሩ ውሉድ" ስለኾኑ "በእንተ-ትሩፋን" ማለት ስለነርሱ የተነገረ ትንቢት ማለት ነው። ሊቃውንቱ ከ፻፶ው የዳዊት መዝሙራት ግማሽ ያኽሉን "ስለ ትሩፋን ተናግሮታል" እያሉ ከትሩፋኑ ሕይወት ጋራ አያይዘው ያኼዷቸዋል። እውነትም ብዙዎቹ መዝሙራት አንድምታ ሳያሻቸው በዘይቤ ቅሉ የትሩፋንን ሕይወት ያንጸባርቃሉ። ለዚህም "ውስተ-አፍላገ-ባቢሎን ህየ ነበርነ ወበከይነ"ን (፻፴፮ኛውን መዝሙር) እና የመሳሰሉትን ማስታወስ ይበቃል።

"ጸሎቱ ለሙሴ ብእሴ-እግዚአብሔር" የሚለው ግን የዚህ መዝሙር ደራሲ ሙሴ እንደነበረ የሚያስመስል አነጋገር ነው። ለዚህ አስተሳሰብ መነሻው የአይሁድ ሊቃውንት መላምት ሲኾን በተለይ የውጮቹ ዘመናውያን ነባብያነ-መለኮት በስፋት የሚከተሉት ነው። ባገራችን ግን አኹን አኹን እንደማናቸውም ሸቀጥ ሳናጣራ ከምናስገባቸው ባህላት ጋራ ተቀላቅሎ የገባ እንጂ ጥንቱን የነበረ አይመስልም። እንዲህ ለማለት የደፈርንበት ምክንያት ባጭሩ፦ የሊቁ ዘር አልያዘውማ! ይኸውም ሊታወቅ መምህራኑ ይህን መዝሙር ሊያኼዱ ሲጀምሩ የሚሉት እንዲህ ነው፦
እግዚኦ ጸወነ ኮንከነ። ስለ ትሩፋን ተናግሮታል። አቤቱ ለልጅ ልጅ አምባ መፀጊያ ኾንኸን...
[በመካከሉም እንዲህ የሚል እናገኛለን፦]
ወመዋዕለ-ዓመቲነኒ ክራማት። ትሩፋን በባቢሎን የሚኖሩት ሰባ ዘመን ነው። ወእመሰ በዝ ሰማንያ ዓም። (ሢራ ፲፷፡-፲።) ከዚያም ዕልፍ ቢል ሰማንያ ዘመን ነው... 
በርግጥ እዚህ "ቀጥፈን" ያመጣናቸው ጥቅሶችም ኾኑ መላ መዝሙሩ ከትሩፋን ታሪክ የዘለለ ትርጕም እንዳላቸው በአንድምታው እንረዳለን። ይኹን እንጂ፤ መዝሙሩ "የሙሴ ጸሎት" እንደነበረ የሚጠቁም አንዳችም ነገር የለም። (በትርጓሜው ውስጥ የሙሴ ስም የተጠቀሰበት አጋጣሚ ቢኖር ስንኳ ይኽ ነው፡- በቊጥር ላይ ያለውን "ወዓለምነሂ ውስተ-ብርሃነ-ገጽከ" የሚለውን ሲተረጕሙ "አንድም...የኛስ [የትሩፋን] ተድላችን የፊትህ ብርሃን ተሥሎበት በተወለደ በሙሴ ጊዜ ቀርቷል" ይላሉ። ይኸውም ቅሉ የችግር ጓዝ የወለደው ዐተታ መኾኑን ወደፊት እናሳያለን።) እንዲህም ስለኾነ እኛም የዚህን መዝሙር ርእስ በዋናነት "በእንተ-ትሩፋን" ብቻ እንደኾነ አድርገን ወስደነዋል። ነገር ግን፤ በአንድምታ የተሰጡትን ርእሱን ዐልፈው የሚኼዱ ቁምነገሮች ልብ ከማድረግ ጋራ በነርሱ ተመርጕዘን ይገለጥልን ዘንድ ያለውንም ምስጢር ሳያመልጠን ለመያዝ ነቅተን እንጠብቃለን። ይቆየን።