በገነት አትክልት ነገር፦() ጣዕም፣ () ልማላሜ፣ () ጽጌ፣ () ሥን፣ () ፍሬ፣ () መዐዛ፣ () ቈጽል፣ ይገኛል። እንዲሁም በመዝሙረ-ዳዊት ነገር፦ () አፍቅሮ-ጸላዕት፣ () ትሕትና፣ () ሃይማኖት፣ () ተስፋ-መንግሥተ-ሰማያት፣ (፭) ተአምኖ-ኀጣውእ፣ () ስርየት፣ () ምጽዋት ይገኛል።

Tuesday, May 31, 2011

እግዚኦ ጸወነ ኮንከነ (ትርጕም 3)

ኢትሚጦ ለሰብእ ለሳር
ወትቤ ተመየጡ ደቂቀ-እጓለመሕያው...
ወዓመቲነኒ ከመ-ሣሬት ይከውና።
ወመዋዕለ-ዓመቲነኒ ክራማት
ወእመሰ በዝ ሰማንያ ዓም
ወፈድፋዶንሰ እምእላ ፃማ ወሕማም
እስመ-ለፈት የውሀት እምኔነ፤ ወተገሠጽነ።
መኑ የአምር ይለ-መቅሠፍትከ
እምግርማ መዐትከ ልቁ።
ከመዝ አርኢ የማነከ 
ለምሁራነ-ልብ በጥበብ።

ባለፈው "...ከኹሉ አስቀድሞ የነበርኽ፤ ዓለምንም አሳልፈኽ የምትኖር አንተ ነኽ 'ኮ! አንተ ነኽና..." በማለት ጅምሩን "ሰብከን" (ሞከር አድርገን) አቆይተነው ነበር። (ባንድምታ ትምርት እንደነገ ጥልቅ ትምርቱ ሊቀጥል እንደዛሬ አርእስተ-ነገሩን ሞክሮ መተው "መስበክ" ይባላል።) እስኪ ባለፈው በሰበክነው ላይ ጥቂት እንቀጥል።

ከኹሉ አስቀድሞ የነበርኽ፤ ዓለምንም አሳልፈኽ የምትኖር አንተ ነኽ 'ኮ! አንተ ነኽና፦ ኢትሚጦ ለሰብእ ለሳርሳርን ለሰው ሰውን ለሳር አሳልፈኽ አትስጠው። አንተ ወትቤ ተመየጡ ደቂቀ-እጓለመሕያው ከገቢረ-ጢአት ወደገቢረ-ጽድቅ፣ ከአምልኮ-ጣዖት ወደ አምልኮ-እግዚአብሔር ተመለሱ፤ እኔም ከመዐት ወደምሕረት እመለስላችዃለኹ ብለኻልና፤ እኛም...ተመልሰናልና አንተም...ተመልሰኽ ይቅር በለን። 
ለነገሩማ ጥንቱን መበደላችን ቅሉ እኛንስ ምን ሊጠቅመን አንተንስ ምን ሊጎዳኽ ወዓመቲነኒ ከመ-ሣሬት ይከውና፦ ዘመኖቻችን እንደሸረሪት የኾኑ ምናምንቴዎች አይደለንምን? ሸረሪት ከእሳት የገባች እንደኾነ አጥንት ጕልጥምት የላትም ቀልጣ ትጠፋለች እኛስ ከሞትን በዃላ መች የት ደረሰ እንባላለን! (እዚህ ላይ ትሩፍ በፍጹም ልቡ አምኗልና አምላኩ "ብሑተ-ህላዌ" እንደነው/እንደኾነ በተረዳው መጠን የራሱም "ንዴተ-ህላዌ" እንዴት ጠልቆ እንደገባው ልብ ይሏል።)

ከዚህ በዃላ ወደጊዜያዊ ችግሩ ተመልሶ "ነቢያት እንደተናገሩ፦ በባቢሎን የምንኖረው ሰባ ዘመን ነው፤ ከዚያም ዕልፍ ቢል ሰማንያ ዘመን ነው። ከሰማንያ ዘመን በዃላ ግን ጻር ጋር ነው፤ ከዚህ ከቀረ መቅረቱ ነውና።" በማለት የምርኮውን ዘመን ይጠቅሳል። ያም ሊኾን የቻለው ባለፈው እንዳተትነው በገዛ ጥፋቱ መኾኑን ይገልጥና የቅጣቱንም አግባብነት እንዲህ ሲል አጕልቶ ይናገራል፦ መኑ የአምር ይለ-መቅሠፍትከ[እንዲያ በድለን] መከራ ባታመጣብን መቅሰፍትኽን የምታመጣበት ይልኽን ማን ባወቀው ነበር።ከዚሁ አያይዞ መከራው በአሕዛብ (በባቢሎናውያን) አማካይነት መምጣቱ በአሕዛብ የበላይነት በሕዝበ እግዚአብሔር (በእስራኤል) የበታችነት ሳይኾን፤ እነርሱም (አሕዛቡ፣ ባቢሎናውያኑ) ፍጡራንኽ እንደመኾናቸው በመሣሪያነት በተጠቀምኽባቸው ባንተው ፈቃድ ነው ለማለት እምግርማ መዐትከ ልቁ፦የተፈጸምነውስ ያንተ ቁጣ ከመገለጡ የተነሣ ነው ይላል። ይኸውም ያንተ ቀኝ ያንተ ሥልጣን ሥራ መኾኑን ከመዝ አርኢ የማነከ ለምሁራነ-ልብ በጥበብ ጥበብን ሕግን ለምናውቅ ለእኛ ግለጥልን በማለት አያይዞ ይለምናል። 

ተመይጥ እግዚኦ እስከ-ማእዜኑ?
ወተናበብ በእንተ-አግብርቲከ... ይቆየን።

No comments:

Post a Comment