ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት አንዱንም አንዱን መጽሐፍ ለመተርጎም ሲነሡ፤ የደራስያኑን የስማቸውን ትርጕም ከሕይወት ታሪካቸው ጋራ ባጭሩ በማብራራት ይጀምራሉ። ከዚያም እንዳስፈላጊነቱ የመጽሐፉን ይዘት ጠቅለል ባለ መልኩ ያስተዋውቃሉ። መጽሐፉ ከአሥራው መጻሕፍት አንዱ የኾነ እንደኾነ፤ ያ መጽሐፍ ሲነበብ ሲተረጎም ከሐዋርያት መድረሱን፤ ሐዋርያትም ፹፩ መጻሕፍት ለቀሌምንጦስ ሲየስረክቡ ያንን መጽሐፍ አንድ ብለው ቆጥረው እንዳስረከቡት ይጠቁማሉ። እንደየመጽሐፉም ጠባይ በየመቅድሙ የሚጨምሯቸው ሌሎች ቊምነገሮች አሉ። እየቀደም እናያቸዋለን።
ወደመዝሙረ-ዳዊት ስንመለስ፤ ሊቃውንቱ ከኹሉ አስቀድመው ዳዊት ማለት ምን ማለት እንደኾነ፤ ለመንግሥት እና ለትንቢት እንዴት እንደበቃ ከተረኩ በዃላ፤ የተሰጡትን ሀብታት ጠቁመው፤ መላው መዝሙራት የሚያተኩሩባቸውን የተወሰኑ አርእስት ይገልጣሉ። ከዚያም እንደማናቸውም ቅዱሳት መጻሕፍት ኹሉ የመዝሙረ-ዳዊት ረብኅ፣ ጥቅም--ማለትም የተጻፈበት ዋና ምክንያት--ለኛ ምክር፣ ተግሣፅ፣ ዕዝናት ሊኾን እንጂ ለከንቱ እንዳይደለ "ወኵሉ ዘተጽሕፈ ለተግሣፀ-ዚአነ ተጽሕፈ። ከመ-በትዕግሥትነ ወበተወክሎ መጻሕፍት ንርከብ ተስፋነ። እንዲል ሮሜ ፲፭፡፬ " በማለት የሐዋርያውን ቃል አስታውሰው ትርጓሜውን ያኼዳሉ።