በገነት አትክልት ነገር፦() ጣዕም፣ () ልማላሜ፣ () ጽጌ፣ () ሥን፣ () ፍሬ፣ () መዐዛ፣ () ቈጽል፣ ይገኛል። እንዲሁም በመዝሙረ-ዳዊት ነገር፦ () አፍቅሮ-ጸላዕት፣ () ትሕትና፣ () ሃይማኖት፣ () ተስፋ-መንግሥተ-ሰማያት፣ (፭) ተአምኖ-ኀጣውእ፣ () ስርየት፣ () ምጽዋት ይገኛል።

Monday, December 27, 2010

መዝሙር ዘዳዊት ሃሌ ሉያ

ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት አንዱንም አንዱን መጽሐፍ ለመተርጎም ሲነሡ፤ የደራስያኑን የስማቸውን ትርጕም ከሕይወት ታሪካቸው ጋራ ባጭሩ በማብራራት ይጀምራሉ። ከዚያም እንዳስፈላጊነቱ የመጽሐፉን ይዘት ጠቅለል ባለ መልኩ ያስተዋውቃሉ። መጽሐፉ ከአሥራው መጻሕፍት አንዱ የኾነ እንደኾነ፤ ያ መጽሐፍ ሲነበብ ሲተረጎም ከሐዋርያት መድረሱን፤ ሐዋርያትም ፹፩ መጻሕፍት ለቀሌምንጦስ ሲየስረክቡ ያንን መጽሐፍ አንድ ብለው ቆጥረው እንዳስረከቡት ይጠቁማሉ። እንደየመጽሐፉም ጠባይ በየመቅድሙ የሚጨምሯቸው ሌሎች ቊምነገሮች አሉ። እየቀደም እናያቸዋለን።

ወደመዝሙረ-ዳዊት ስንመለስ፤ ሊቃውንቱ ከኹሉ አስቀድመው ዳዊት ማለት ምን ማለት እንደኾነ፤ ለመንግሥት እና ለትንቢት እንዴት እንደበቃ ከተረኩ በዃላ፤ የተሰጡትን ሀብታት ጠቁመው፤ መላው መዝሙራት የሚያተኩሩባቸውን የተወሰኑ አርእስት ይገልጣሉ። ከዚያም እንደማናቸውም ቅዱሳት መጻሕፍት ኹሉ የመዝሙረ-ዳዊት ረብ፣ ጥቅም--ማለትም የተጻፈበት ዋና ምክንያት--ለኛ ምክር፣ ተግሣፅ፣ ዕዝናት ሊኾን እንጂ ለከንቱ እንዳይደለ "ወኵሉ ዘተጽሕፈ ለተግሣፀ-ዚአነ ተጽሕፈ። ከመ-በትዕግሥትነ ወበተወክሎ መጻሕፍት ንርከብ ተስፋነ። እንዲል ሮሜ ፲፭፡ " በማለት የሐዋርያውን ቃል አስታውሰው ትርጓሜውን ያኼዳሉ።

እዚህ ላይ በተለይ አንድ ቊም ነገር ልብ ብለን እንለፍ። ከበሓውርተ-ዓለም እስራኤልን መርጦ ሕዝቡ ያደረጋቸው አምላክ፤ ከሕዝበ-እስራኤል ደግሞ ዳዊትን መርጦ ከፍ ከፍ አድርጎታል፤ አንግሦታል። (መዝ ፹፡፲) ታዲያ ለእስራኤል ምርጥነት፣ ለዳዊትም ልዕልና (የምርጥ-ምርጥነት) ምክንያቱ፦ ዘር፣ ደም፣ አጥንት፣ ጅማት፣ መልክ፣ የደምግባት፣ እንደነዚህም ያለ ሌላ  ኮተት ሳይኾን፤ ሃይማኖት፣ ቅንነት፣ ትሕትና፣ የውሀት፣ እሊህንም የመሳሰለው ነው። "ሥኖ ለያዕቆብ ዘአፍቀረ" (የያዕቆብን ምግባር ሃይማኖት የወደደ እሱ ነው። መዝ፮፡ ) "ወረዮ ለዳዊት ገብሩ...በየውሀተ-ልቡ...በጥበበ-እደዊሁ" (...መረጠው።... የውሀትን በያዘ ልቡናው...በፈሊጥ ቃሉ። መዝ ፸፯፡፸) "ተዘከሮ እግዚኦ ለዳዊት ወለኵሉ የውሀቱ" (...ሕግ መጠበቁን፣ ቅንነቱን። መዝ ፻፴፩፡፩)

ዳዊት ንጉሥ ብቻ ሳይኾን ነቢይም ማሕሌታዊም ነው። መዝሙሩም እንደናቡከደነጾር ያሉ ሰነፎች ራሳቸው እንዲመለኩበት ያስቀነቀኑት ዐይነት ሳይኾን፤ በሰማይም በምድርም ያሉ ኹሉ ለእውነተኛው አምላክ በሚገዙበት በ"ሃሌ ሉያ" የተቃኘ ነው፤ "ዘውእቱ ብሂል" (ሃሌ ሉያም ማለት)፦ "ንወድሶ ለዘሀሎ እግዚአብሔር ልዑል" (የነበረ-ያለ-እና-የሚኖር ልዑል እግዚአብሔርን እናመስግነው) ማለት ነው። በነጠላው ሲተረጎም፦ "ሀልሉ ያህ = ሰብሑ እግዚአ (እግዚአብሔርን አመስግኑ)" ነው።

ይህ እንዲህ ነው፤ እንዲህም ስለኾነ ርእሱ፦

"ፍካሬ ዘጻድቃን ወዘጥኣን
መዝሙር ዘዳዊት ሃሌ ሉያ" ይላል።

ይኸውም ባንድምታ ሲብራራ፦

  • የጻድቃንን እና የጥኣንን ግብር ለይቶ የሚናገር መጽሐፍ ይህ ነው። 
  • አንድም ጻድቃንን በለውዝ በገውዝ፣ ጥኣንን በዕፅ ከንቱ መስሎ የተናገረው መጽሐፍ ይህ ነው።
  • ይኸውም የዳዊት መጽሐፍ ነው።
  • ዳዊት በበገና፣ በገና እየደረደረ የተናገረው።
  • አንድም ዳዊት በመዝሙር የተናገረው መጽሐፍ ይህ ነው።


አነሣሥቶ ላስጀመረን ለልዑል እግዚአብሔር ክብር ምስጋና ይግባው። አተጋግቶ እንዲያስፈጽመንም ቅዱስ ፈቃዱ ይኹንልን። አሜን። ይቆየን።

2 comments: