በገነት አትክልት ነገር፦() ጣዕም፣ () ልማላሜ፣ () ጽጌ፣ () ሥን፣ () ፍሬ፣ () መዐዛ፣ () ቈጽል፣ ይገኛል። እንዲሁም በመዝሙረ-ዳዊት ነገር፦ () አፍቅሮ-ጸላዕት፣ () ትሕትና፣ () ሃይማኖት፣ () ተስፋ-መንግሥተ-ሰማያት፣ (፭) ተአምኖ-ኀጣውእ፣ () ስርየት፣ () ምጽዋት ይገኛል።

Tuesday, May 3, 2011

እግዚኦ ጸወነ ኮንከነ (ትርጕም)

"እግዚኦ ጸወነ ኮንከነ"ን (፹፱ኛውን መዝሙር) እዚህ ለጀመርነው ሥራ መቃናትም ኾነ ለሕይወታችን እንድንጸልየው በማሳሰብ ንባቡን በምልክት አዘጋጅተን ከኛው ክታባችን ጋራ አያይዘን አቅርበነዋል (አኹንም በድጋሚ አያይዘነዋል)። በቀደመው ክታባችን እንድናያይዘው መነሻ የኾነን "ፈጻሚ እንጂ ጀማሪ ብቻ አያድርጎት" የሚለው ያንድ ወዳጃችን ምኞት እና ጸሎት ነበር።  አኹን ደግሞ የትርጓሜ ልምምዳችንን በዚሁ መዝሙር ለመጀመር ስላሰብን ዘሩን በቅርቡ እንድናገኘው ነው። እነሆ ዘሩን ደጋግመን እያነበብን ትርጕሙንም ቀስ እያልን እናኺደው።

በዚች ክታብ ሊያጋጥሙን የሚችሉትን የሚከተሉትን ስያሜዎች ልብ እንድንላቸው፦ 
  • ማኼድ = the process of interpretation
  • ዘር = the verse/passage to be interpreted
  • የሊቅ ዘር = the version (of the verse/passage) preferred by scholars
  • ዘይቤ = literal interpretation
  • አንድም = introduces alternative interpretation
  • ቀጠፋ = excerption
  • ርእስ/አርእስት = title/theme
  • በእንተ- = on/about...
"እግዚኦ ጸወነ ኮንከነ" በርእሱ "በእንተ-ትሩፋን፤ ጸሎቱ ለሙሴ ብእሴ-እግዚአብሔር" ይላል። ይህም ማለት፦ (1) ስለ-ትሩፋን፤ (2) የእግዚአብሔር ሰው የሙሴ ጸሎት፤ ማለት ነው። "ትሩፋን" የሚባሉት በባቢሎን ምርኮ "አበው አልቀው የቀሩ ውሉድ" ስለኾኑ "በእንተ-ትሩፋን" ማለት ስለነርሱ የተነገረ ትንቢት ማለት ነው። ሊቃውንቱ ከ፻፶ው የዳዊት መዝሙራት ግማሽ ያኽሉን "ስለ ትሩፋን ተናግሮታል" እያሉ ከትሩፋኑ ሕይወት ጋራ አያይዘው ያኼዷቸዋል። እውነትም ብዙዎቹ መዝሙራት አንድምታ ሳያሻቸው በዘይቤ ቅሉ የትሩፋንን ሕይወት ያንጸባርቃሉ። ለዚህም "ውስተ-አፍላገ-ባቢሎን ህየ ነበርነ ወበከይነ"ን (፻፴፮ኛውን መዝሙር) እና የመሳሰሉትን ማስታወስ ይበቃል።

"ጸሎቱ ለሙሴ ብእሴ-እግዚአብሔር" የሚለው ግን የዚህ መዝሙር ደራሲ ሙሴ እንደነበረ የሚያስመስል አነጋገር ነው። ለዚህ አስተሳሰብ መነሻው የአይሁድ ሊቃውንት መላምት ሲኾን በተለይ የውጮቹ ዘመናውያን ነባብያነ-መለኮት በስፋት የሚከተሉት ነው። ባገራችን ግን አኹን አኹን እንደማናቸውም ሸቀጥ ሳናጣራ ከምናስገባቸው ባህላት ጋራ ተቀላቅሎ የገባ እንጂ ጥንቱን የነበረ አይመስልም። እንዲህ ለማለት የደፈርንበት ምክንያት ባጭሩ፦ የሊቁ ዘር አልያዘውማ! ይኸውም ሊታወቅ መምህራኑ ይህን መዝሙር ሊያኼዱ ሲጀምሩ የሚሉት እንዲህ ነው፦
እግዚኦ ጸወነ ኮንከነ። ስለ ትሩፋን ተናግሮታል። አቤቱ ለልጅ ልጅ አምባ መፀጊያ ኾንኸን...
[በመካከሉም እንዲህ የሚል እናገኛለን፦]
ወመዋዕለ-ዓመቲነኒ ክራማት። ትሩፋን በባቢሎን የሚኖሩት ሰባ ዘመን ነው። ወእመሰ በዝ ሰማንያ ዓም። (ሢራ ፲፷፡-፲።) ከዚያም ዕልፍ ቢል ሰማንያ ዘመን ነው... 
በርግጥ እዚህ "ቀጥፈን" ያመጣናቸው ጥቅሶችም ኾኑ መላ መዝሙሩ ከትሩፋን ታሪክ የዘለለ ትርጕም እንዳላቸው በአንድምታው እንረዳለን። ይኹን እንጂ፤ መዝሙሩ "የሙሴ ጸሎት" እንደነበረ የሚጠቁም አንዳችም ነገር የለም። (በትርጓሜው ውስጥ የሙሴ ስም የተጠቀሰበት አጋጣሚ ቢኖር ስንኳ ይኽ ነው፡- በቊጥር ላይ ያለውን "ወዓለምነሂ ውስተ-ብርሃነ-ገጽከ" የሚለውን ሲተረጕሙ "አንድም...የኛስ [የትሩፋን] ተድላችን የፊትህ ብርሃን ተሥሎበት በተወለደ በሙሴ ጊዜ ቀርቷል" ይላሉ። ይኸውም ቅሉ የችግር ጓዝ የወለደው ዐተታ መኾኑን ወደፊት እናሳያለን።) እንዲህም ስለኾነ እኛም የዚህን መዝሙር ርእስ በዋናነት "በእንተ-ትሩፋን" ብቻ እንደኾነ አድርገን ወስደነዋል። ነገር ግን፤ በአንድምታ የተሰጡትን ርእሱን ዐልፈው የሚኼዱ ቁምነገሮች ልብ ከማድረግ ጋራ በነርሱ ተመርጕዘን ይገለጥልን ዘንድ ያለውንም ምስጢር ሳያመልጠን ለመያዝ ነቅተን እንጠብቃለን። ይቆየን።


No comments:

Post a Comment